Monday, July 7, 2014

መለያየት የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን አደጋ





የአንድ ምዕመን አስተያየት
(አንድ አድርገን ሰኔ 30 2006 ዓ.ም )፡- መስቀል ለእኛ ለምናምንበት ድህነትን ያገኘንበት፤ ተለያይተው የነበሩትን እግዚአብሔርና ሰዎችን እንዲሁም ሰዎችና ሰዎችን አንድ ያደረገና ያስታረቀ ለሰው ልጆች ሰላምን፤ ፍቅርን፤ እርቅን፤ አንድነትን ፤ ጽድቅን ያደለ ሁሌም ከልባችን የማይጠፋ ውለታ የተዋለበት ነው፡፡ ይሁንና ጌታ በመስቀሉ ያደለንን ነጻ ስጦታ ገፍተን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተቃራኒው ጠብንና መለያየትን እያስፋፋን ወደ ከፋ ደረጃ እየሄድን እንገኛለን፡፡

ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ዘመናት ብዙ ፈተናዎችና አደጋዎችን አልፋለች፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በእግዚአብሔር እርዳታ አባቶቻቸንንና ምእመኖቿ በጋራ ባደረጉት ከፍተኛ ተጋድሎ የተነሳ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ብዙ የምንታወቅበት ነገር ምንም አይነት ልዩነት ቢኖረን ሀገርንና ሃይማኖትን ሊነካ የውጭ ጠላት ሲመጣ ተባብረን አሳፍረን በመመለሳችን ነው፡፡ ይህ የውስጥ አንድነት ለጥንካሬያችን መሰረቱ ነው፡፡


ቤተ ክርስቲያን ባሁኑም ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ተጋርጠውባታል፡፡ ከነዚህም አንዱ ከመናፍቃን በተለያየ ስልት እየተከፈተ ያለው ግልጽም ሆነ ስውር ወረራ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ከፖለቲከኞች የሚደርስባት ሌላ ፈተናም አለ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም -አማንያንና እንዲሁ የራሳቸውን ፈተና በቤተክርስቲያን ላይ ጋርጠዋል፡፡ እነዚህና የመሳሰሉት ሌሎች ውጫዊ አደጋዎች የቱንም ያህል የጠነከሩ ቢሆኑ ክርስቲያንና ሚስማር ሲመቱት ይጠብቃል› እንዲሉ ያጠነከሩን ይሆን እንጂ ሊያጠፉን አይችሉም፡፡

ባሳለፍናቸው ጊዜያት እንደተመለከትነው አብዛኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ  አደጋ ከውጪ የሚመጣ ብቻ ሳይሆን ከውስጣችን የሚመነጭ ሆኖ እናገኝዋለን፡፡በአሁን ወቅት ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አደጋ ጋርጠው ያሉት ከላይ የተጠቀሱት ውጫዊ ፈተናዎች ብቻ ሳይሆኑ ከውስጥ የሚመነጩ ችግሮች ጭምር ናቸው፡፡ ክፋቱ እነዚህ በውስጣችን ያሉ ፈተናዎች ራሳቸው ከሚጋርጡት አደጋ በመለስ ለውጪያው ፈተናዎች ጥቃት አሳልፈው ይሰጡናል፡፡ እነዚህን ፈተናዎች መቋቋም ከቻልን ከውጭ የሚመጣውንም አደጋ መከላከል ይቻላል ፤ ይህ ካልሆነ ግን ከውስጥ ያለው ችግር ጊዜውን ጠብቆ በማመርቀዝ ላልተፈለገ ለውጭ አደጋ አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ 
  
ለመዘርዘር ከሚታክቱት የውስጥ ቸግሮቻችን መከከል ለቤተ ክርስቲያን አደጋ የሆነው እየሆነም ያለው እርስ በእርስ መለያየታችን ነው፡፡ በውስጣችን ከፍተኛ የሆነ ክፉ የመከፋፈል መንፈስ ተዛምቷል፡፡ በዘር፤ በቡድን ፤ በማኅበር ፤ በሰፈር ፤ በጓደኝነትወዘተ መከፋፈል እጣ ፈንታችን ሆኗል፡፡ ክፍፍሉ በፓትሪያርኮች ፤  በሲኖዶስ ፤  በጳጳሳት ፤  በካህናት ፤ በዲያቆነት ፤ በሰባኪያን ፤ በዘማሪያን ፤ በሰንበት ተማሪዎች ፤ በሰበካ ጉባኤ መካከል ሆኖ ይታያል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማን ያልተከፋፈለ አለ?፡፡ ሌላው ቀርቶ በዓለም ሙት ናቸው በሚባሉት በመነኮሳት ዘንድ ሳይቀር፡፡ ክፍፍሉ በብሔር ይጀምርና ሰፈርና ጓደኝነት ጋር ይደርሳል፡፡ ከላይ ከሲኖዶስ ተነስቶ እስከ ታች ጽዋ ማኅበር ይወርዳል፡፡ በዚህም የተነሳ በሃሳቦች ራሱ መስማማት የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ቋንቋችንም ተደበላልቋል ፤ መደማመጥም ሆነ መተማመንም አልቻልንም፡፡ ሃሳቦች ሲነሱ የሚታየው ስለሃሳቡ ጠቃሚነትና ጎጂነት ሳይሆን ሃሳቡን ያቀረበው ማን ነው? የማን ወገን ሃሳብ ነው? የሚል ጥያቄ ነው ፡፡ 

በአጭር ቋንቋ ሃሳቦች ራሳቸው በዘር ፤ በቡድን ፤ በማኅበር ፤ በሰፈር በጓደኝነት ተፈርጀዋል፡፡ ከእነንትና ወገን/ቡድን/ማኅበር ከቀረበ በፍጹም ለቤተ ክርስቲያን አይጠቅምም፡፡ ከነዚህኞች እንትናዎች ብቻ ነው ጠቃሚ ሃሳብ ሊቀርብ የሚችለው በማለት እርግጠኛ የሆኑ ሰዎች በዝተዋል፡፡  የራስ ቡድን ካጠፋ ተሳስቶ ነው፡፡ የሌላኛው ቡድን ሲያጠፋ አውቆ ነው ስውር አጀንዳ ስላለው እርምጃ ይወሰድበት ይባላል፡፡ በሚያሳፍር ሁኔታ ዘር  ቆጠራ  በሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር መዋቅር ተንሰራፍቷል፡፡ ለሚካሄዱ ክፉ ስራዎች ሁሉ መሸፈኛው ዘር ሆኗል፡፡ .እንትን የሚባለው ማኅበር እስካሁን አመራር የነበረው ከዚህ ዘር ስለሆነ ያኛውም እንዲደርሰው መንግሥት በመጠየቁ እንትና ከእንትን ዘር ተሾመ የሚሉ ወሬዎችን መስማት እንደ ተራ ነገር እየተቆጠረ ነው፡፡
 
ካህናቱም እንዲሁጎጃሜ ጎንደሬወዘተ በሚል ክፍፍል በውስጣዊ ሽኩቻ ላይ ሲሆኑ የራሳቸው ወገን የሆኑ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችን ለማሾም ጥረት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከሌላ ዘር ከተሾመባቸውና ካልተስማማቸው ለማስነሳት የማይፈነቅሉት ድንጋይ አለመኖሩ ይስተዋላል ፡፡ አንድ ከጎጃም የሆነ ካህን በሙስና ተዘፍቆ ከአገልግሎት ቢታገድና የሚያገለግልበት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ጎንደሬ ቢሆኑ እሱ የሚለው ‹‹በሙስናዬ ታገድኩ›› ሳይሆን አስተዳደሪው ጎንደሬ ስለሆኑ አገዱኝ ይላል፡፡ በሌላ በኩል አስተዳዳሪው ጎጃሜ ቢሆኑ ወይም እሱ ጎንደሬ ቢሆን ላይታገድ ይችላል፡፡ ሲጀመር ቤተ ክርስቲያን ተጠግቶ የሚሰርቅ ካህን ከመላእክት ወገንም ቢሆን መታገድ ነው የሚኖርበት፡፡ እንደው ለማሳየት ያህል ዘርን መሰረት አድርጎ ያለውን ክፍፍል ለአብነት ያህል አነሳን እንጂ በዚህ አጭር ጽሁፍ ተዘርዝረው የማያልቁ ግን ሁላችን የምናውቃቸው ብዙ መለያያ ምክንያቶች አሉ፡፡  ክፍፍሉን ልዩ የሚያደርገውና የሚገርመው ሌላውን የማይከፋፍለው ነገር ሁሉ እኛን መከፋፈል መቻሉ ነው፡፡ ምናልባትም ይህ የሰይጣን ውጊያ ስለሆነ ይሆናል፡፡

ይህን አስቀያሚ መለያየት/መከፋፈል የሚባል ነገር ከየት እንዳመጣነው ከየትስ እንደወረስነው ግራ የሚገባ ነገር ነው፡፡ ሲጀመር ለሁሉ ነገራችን መመሪያችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ወይም የቀደሙ አባቶቻችን በተግባር ያስተማሩን ይህን አልነበረም፡፡ ይልቁንም መጽሐፍም ሆነ አባቶቻችን ያስተማሩን የአይሁድ ሰው ፤ የግሪክ ሰው ፤ የሮማ ሰው ፤ የግብጽ ሰው ፤ የኢትዮጵያ ሰው እያልን ዘረኛ እንዳንሆንና እኔ የአፕሎስ እኔ የኬፋ ነኝ እያልን እንዳንከፋፈል ነበር፡፡ ዘራችን ክርስትና ሀገራችንም በሰማይ እንደሆነ ስንሰበክ አንዳንዶቻችንም ስንሰብክና ስንዘምር ኖረናል፡፡ አባቶችም ስለ አንድነትና ኅብረት ሲጸልዩ ኖረዋል፡፡ መጽሐፍ  ‹‹እርስ በእርሷ የተከፋፈለች መንግሰት ደሞ ትወድቃለች፡፡›› ይላል፡፡ ለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥላት አሁን በስፋት እየታየ ያለው የርስ በርስ መከፋፈል ነው የምንለው፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳውያን የመለያየትን አደጋ በአይናችን በብሌኑ በራሳችን ተፈጽሞ አይተናል፡፡ ባንድ ወቅት ከወደ ሰሜን አሜሪካ አንድ ድንቅ ዜና ተሰማ፡፡ አቡነ መርቆሪዎስ ያለ አግባብ ከስልጣናቸው መባረራቸውን ገልጸው እውነተኛው ፓትሪያክ እኔ ነኝ አሉ፡፡ አቡነ ጳውሎስም እንዴት ሆኖ አሉ፡፡ በአጭር ቋንቋ አቡነ መርቆርዮስና አቡነ ጳውሎስ ተለያዩ፡፡ ሁለቱም ራሳቸውን ትክክለኛ ፓትሪያርክ አድርገው ሌላውን ህገ ወጥ አድርገው አወጁ፡፡ እንዱ የሌላውን ሲኖዶስ ህገወጥ አለ፡፡ እርስ በእርሱ ተወጋገዙ ተገዛዘቱ፡፡ ውጉዝ ከመ አርዮስ ተባባሉ፡፡ የዚህ የመለያየት አደጋ ከግለሰቦች አልፎ ቤተ ክርስቲያኗን ሊንጥ የሚችል መሆኑን ማየት የተጀመረው አቡነ መርቆርዮስ የራሳቸውን ጳጳሳት በሰሜን አሜሪካ ፤ በአውሮፓ አህጉረ ስብከቶች ሲሾሙና ተቀባይነት ሲያገኙ ነው፡፡  ሁለቱም የክፍፍሉ ራሶች ወደማይቀረው ዓለም መጓዛቸው እንደማይቀር ቀድሞ ራሳቸው ያውቁታል ፤ ነገር ግን ለትውልድ ነቀርሳ የሆነውን ክፍፍል ትተው ማለፋቸው ፤ መፍትሄ ማስቀመጥ አለመቻላቸው ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለሌላ ክፍፍል መንገድ ጠራጊ መሆናቸውን  እያስታወሰ ትውልድ ያነሳቸዋል፡፡ 318ቱን ሊቃውንት ዘመን ተሻግሮ ለአንዲት ቤተክርስቲያን አንድነት የሰሩትን ሥራ ትውልድ አሁን ላይ እንደሚነሱ ሁሉ ፤ አሁንም እኚህ ሁለት አባቶች ለቤተ ክርስቲያን እና ለምዕመኗ መለያየት ዘመን ተሻግሮ መነሳታቸው አይቀሬ ነው፡፡ እኛም በአሁኑ ሰዓት የምንገኝ ምዕመናን ካለፈው መማር ለአንድነትም መጣር ይገባናል፡፡ ምንም ቀብራችን ቢያምር ሥራችን ለትውድል መቀመጥ መቻሉን በመልካምም ይሁን በሌላ መልኩ መነሳታችን አይቀሬ ነው፡፡ ከሁሉም በፊት መልካምነትና ጥሩ ሥራ ለራስ ነውና፡፡

አንድ ሰባኪ ወይም ዘማሪ ወይም ካህን በአሁኑ ወቅት ሰሜን አሜሪካ ሄዶ እንደልቡ የፈለገበት ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል አይችልም፡፡ ምክንያቱም አብያተ ክርስቲያናቱም በሁለቱ ፓትሪያርኮች ጎራ ተከፋፍለዋል፡፡ የማን ደጋፊ ነህ?  የሚለውን ጥያቄ መመለስ የታዋቂ ሰባኪዎችና ማኅበራት ሳይቀር ራስ ምታት ሆኗል፡፡ አሁን ላይ ያለው ይህ ክፍፍል በዘመን ርቀት ቤተ ክርስቲያኗን ላለመክፈሉ ምን ዋስትና አለ? ይህ የሚያሳየን እንደ ቀላል የተጀመረ መለያየትና ክፍፍል ለቤተ ክርስቲያን አደጋ ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡

በእኛ መለያየት በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰው አደጋ የሚያሳስበን ከሆነ ተከፋፍለን በሩቁ ከመተጋተግ ጠጋ ብለን መወያየት የግድ የሚለን ወቅት ላይ እንገኛለን ፡፡ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ቡድን/ማኅበር/  ደጋፊ ወይም አባል ሆነን ተለያይተናል፡፡ ሌሎቻችን መለያየቱን እንዲሰፋ አድርገናል ወይም ዝም ብለን አይተናል፡፡ መለያየት ሃጢያት እንደሆነ ሁላችንም የማንስተው ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ቤተ ክርስቲያንን በድለናል  ፤ እግዚአብሔርንና ምእመናንን አሳዝነናል፡፡ስለሆነም ያለፈውን በክፋት፤ በበደል፤ በመራርነት ፤ በጠብ ፤ በመለያየት የኖርንበት ዘመንን አቁመን ወደ እርቅ ፤ ወደ ሰላም፤ ወደ ይቅርባይነትና ወደ አንድነት መመለስ ወደ ጽድቅ የመመለስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንንም ከአደጋ የመጠበቅ ጉዳይም ይሆናል፡፡

ከዲያብሎስ ወጥመድ ያመልጡ ዘንድና በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት በእርሱ መንግሥት ዘለዓለማዊ ሕይወትን ያገኙ ዘንድ በንስሐ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ለመመለስ የሚፈልጉትን ሁሉ በምህረትና በርህራሄ መቀበል ይገባል፡፡ ራሱን ከእውነት የሚለየውን ሰው የሚከተለው ቢኖር የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፡፡ ሐሰትን ከሚናገርና ከሚያስተምር ሰው ራሱን የማይለይ ሰውም እርሱ በሲኦል ይፈረድበታል፡፡ መልካም ከሆነው እንዳንለይ ክፉ ከሆነው ደግሞ እንድንሸሽ ግዴታ ነውና፡፡ ነገር ግን ሁላችሁም መከፋፈል በሌለበት በአንድ ልቡና ፣ ሙሉ ፈቃድ ባለው ሕሊና አንድ ሁኑ፡፡ በሰላማችሁ ጊዜም ሆነ በችግር ላይ ስትሆኑ፣ በሐዘንም ሆነ በደስታችሁ ጊዜ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ሁል ጊዜ ተመሳሳይ አመለካከት እንዲኖራችሁ ያስፈልጋል፡፡ሰውነታችሁን እንደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ጠብቁ፡፡ አንድነትን ውደዱ፤ መለያየትን ግን ፈጽማችሁ ተጸየፉ፡፡

ግን እኛ ኦርቶዶክሳውያንን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሰላምን፤ ፍቅርንና እንድነትን በመስጠት የዋለልንን ውለታ እንዳናስተውል አዚም ያደረገብን ማን ነው ? የመስቀሉ ብርሃን ሁላችን ላይ አርፎ ውስጣችን ያለውን የመለያየት፤ የጠብና የመራርነት ክፉ መንፈስ አስወግዶ  አምላክ አንድነትን ፤ ሰላምንና ፍቅርን ያድለን፡፡


9 comments:

  1. AMEN; Abune petros tekmtewubet yeneberew member lay endetekemetu endistewulu le abatochachin libona yistlin

    ReplyDelete
  2. Dear brothers and sisters,
    This situation is our generation big head ache and a bitter war declared by the Devil and his followers against our Church. We should do our best: 1) by fighting against, that is telling to all that such division by ethnicity is a poison for us and our church and, 2) by praying.
    Redeate Egziabehere Kehulachin gar yehun. Amen

    ReplyDelete
  3. ከታላላቆች አባቶቻችን እስከ ተራው ምዕመን በሁሉም ላይ በየደረጃው ችግር አለብን።ለፍቅረ እግዚአብሔር ያለመሸነፍ,ለስጋች ፍላጎት ሉጋም ማጣት,ሆዳምነት አሸንፎናል።ዓይነልቡናችንን ያብራልን:ፖለትከኞችን(ዘረኞችን) የስታግስልን።አሜን!!!

    ReplyDelete
  4. በመሰረተ ሃሳቡ እስማማሎሁ ብዙ ጊዜ ከሚለጠፉት/ከሚለቀቁ ፅሑፎች የተሻለ ነው ብየ አስባሎሁ
    መንጋው ነኝ

    ReplyDelete
  5. Yemeleyayetu minchoch bzu bihonum kebzuwochu andu enante mehonachhu astewlachhu yhon?!!!!

    Ye biete kirstian fetena be fiqrna be tselot lemeftat kememoker ylq be tlachana be qalat bzat endifeta tasbalachhu....

    ewqet be lemenfesawi brtat kalteteqemubet esat hono endemibala be enantem awekut ... !!!

    Yebiete kirstian qinat fiqrna tselot bemastemar ye Egziabher ej tezergta sra endtisera yadergal enji ye milas hayl ye fiqrna tselot ablto ye Egziabhern ej kemesrat atmelsm! !!

    ReplyDelete
    Replies
    1. እንዳንተ መንጋውን የተቀላቀለው ተኩላ ነው የበጠበጠን።

      Delete
    2. ytetsafewun anbibehewal?ezihu eko "እንዳንተ መንጋውን የተቀላቀለው ተኩላ ነው የበጠበጠን" bileh meferej jemerik.

      Delete
  6. ቃለ ህይወት ያሰማህ። ጽሑፉን በጥሞና ላነበበው ሰው በጣም ጥሩ ነው። ነገር ግን አብዛኛው አንባቢ ምእመን በአቡነ መርቆሪዎስና አቡነ ጳውሎስም ምክንያት በተለኰሰው እሳት እረመጥ ውስጥ ስላለ ጸሐፊውን ከመኮነን ወደ ኋላ አይልም። ምክንያቱም " ምን ተባለ ሳይሆን ማን ምን አለ " የሚለውን ሲለሚመረምር ነው።

    ReplyDelete