Saturday, April 11, 2015

ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ጥናት ለምን?




Source :- http://www.dw.de
ከማንተጋፍቶት ስለሺ እና  ከነጋሽ መሐመድ

በግእዝ የተጻፉ ጥንታውያን የብራና መዛግብት በኢትዮጵያ ለሃይማኖት ከሚሰጡት አገልግሎታቸው ባሻገር ሌሎች አገልግሎቶችንም በመስጠት ለዘመናት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በተለይ መጻሕፍቱ ላይ የሠፈሩት ጽሑፎች ከሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ይዘታቸው ባሻገር በየዘመናቱ የነበሩትን ማኅበራዊ ክስተቶች ያመላክቱ እንደነበረም በጥናታዊ ጽሑፎች የተረጋገጠ ነው።
 
በባህር ዳር ከተማ ከመጋቢት 22 እስከ 23 ቀን 2007 ዓም በተኪያሄደው ኹለተኛው የግእዝ ሀገር ዐቀፍ ጉባኤ ላይ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ነበር። «ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ /ቤት» በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነው።
በባህል እና ቱሪዝም አዘጋጅነት ባህር ዳር ከተማ ውስጥ በተከናወነው ኹለተኛው የግእዝ ሀገር አቀፍ ጉባኤ ላይ በርካታ ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን አቅርበዋል። «ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ሰነዶች እንደ ምዝገባና ማረጋገጫ /ቤት» በሚል ርእስ የተሰናዳውን ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ናቸው።


ጥንታዊ የብራና ጽሑፍ በግእዝ ቋንቋ
የዲያቆን ዳንኤል ጥናት ያተኮረው ጥንታውያኑ የብራና መጻሕፍት ከተጻፉበት ቀዳሚ ዓላማ ባሻገር ለሀገሪቱ ያበረከቱት ታላቅ አስተዋፅዖ ላይ ዳሠሣ ማድረግ ነው። ዲያቆን ዳንኤል ጥናታቸውን ሲያኪያሄዱ ግብረ-ኃማማት፣ መጸሐፈ ሐዊ፣ ነገረ-ማሪያም የተሰኙ ታላላቅ መጻሕፍትን እንደመረመሩ ጠቅሰዋል። በመጻሕፍቱ መጀመሪያ እና መጨረሻ በሚገኙ ባዶ ቅጠሎች፣ በኅዳጎቻቸው በግርጌ እና በራስጌዎቻቸው በሚገኙ ክፍት ቦታዎች ላይ የሠፈሩ የተለያዩ ውሎችን ለመቃኘት ሙከራ እንዳደረጉ ገልጠዋል።

ጥንታውያኑ ጽሑፎች ከዛሬ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ በሀገሪቱ የነበረውን የዘመኑ ታሪክ በተለይ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ታሪክ የሚያሳዩ እንደኾኑ ተጠቅሷል። ለጥናታቸው ግብዓት የተጠቀሙት ጽሑፎች በዓፄ ዮሐንስ ዘመን፣ በዓፄ ቴዎድሮስ ዘመን፣ በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን የነበሩትን ውሎች የሚቃኙ እንደኾኑ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገልጠዋል። እስኪ በጥንታውያን መጻሕፉቱ ውስጥ ከሰፈሩት ውሎች መካከል ለአብነት ያኽል የሚከተለውን እናሠማችሁ።

ጣና ሐይቅ፥ ባሕር ዳር
«በዘመነ ማርቆስ ዓጼ ቴዎድሮስ መንግሥት በመልአከ ፀሐይ ማሕሉ አለቅነት ኃብቱ ኃይሉ ሥራ ሲሠራ በከተማ ያለውን ሪሜን ለካብቴ እንግዳ ሰጥቼአለሁ። ዳዊት ይድገምልኝ ብለዋል። መሳክርቱ ድብ ባሕር ደብተራ ተክሌ ቄስ ተስፋዬ ቄስ ሣሕሌ፣ ቄስ ኃይሉ፣ ቄስ ወልዱ፤ ወረቀት ያመጡ የቍስቋም አዛዥ አፈወርቅ ናቸው። ከልቅሶው የነበሩ ወረቀት ሲነበብ አጣጣሞች ቊስቋሞች ናቸው። መልአከ ፀሐይ ፆታ ኃይሉ ነበሩ። ኃብቱ ስኂንም ካብቴ እንግዳ የቃል ኪዳን ልጄ ነው። ወንድሜ የሰጠውን ይዞ እኩሌታ ሪሜን ጠብቆ ለልጆች ይስጣቸው፤ አደራ አባት ይሁናቸው ብለዋል። በዘመነ ማቴዎስ ዓፄ ጓሉ መንግሥት በመልአከ ፀሐይ እንግዳ አለቅነት ያለቃ ኃብቱ ልጅ ዮሐንስ ሪሜን እፃየን ከኃብቱ ኃይሉ ሰጥቻለሁ ብለዋል። መሳክርቱ አለቃ ተክለ ሃይማኖት አሳዬኸኝ፣ ክንፉ አሳዬኸኝ፣ ወልደ ሚካኤል በቀረው ደብሩ።»

የመጀመሪያው የግእዝ ጉባኤ ቀደም ሲል የተሰናዳው በትግራይ አኲሱም ውስጥ ነበር። የዘንድሮውን የባህር ዳር ኹለተኛው የግእዝ ጉባኤ ያዘጋጀው የባሕል እና ቱሪዝም ሚንስትር መሥሪያ ቤት ነው። የመሥሪያ ቤቱ ሚንስቴር ድኤታ ሙሉጌታ ሠዒድ ጉባዔውን ዘንድሮ ለምን ማዘጋጀት እንደፈለጉ ይጠቅሳሉ።

ጥንታዊ የብራና ጽሑፍ በግእዝ ቋንቋ
ወደ ጥናታዊ ጽሑፉ እንመለስ። በእርግጥ ከመቶ ዓመታት በፊት በተጻፉት በእነዚህ ጥንታዊ የብራና ላይ ጽሑፎች የሠፈሩ ውሎች በተወያዮች መካከል አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮችን አሟልተው ይኾን?
በባህር ዳሩ ኹለተኛው የግእዝ ጉባኤ ተሳታፊ የነበሩት የባሕልና ቱሪዝም ሚንስቴር ድኤታ ሙሉጌታ ሠዒድ ወደፊት ግእዝን ጨምሮ ጥንታዊ ቋንቋዎች ላይ የተጠናከረ ጥናት እንዲካሄድ መሥሪያ ቤታቸው ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በጥናታዊ ጽሑፉ ለአብነት ካካተታቸው ጥንታዊ ጽሑፎች መካከል የሚከተለውን እናሠማችሁ። ውሉ በመሬት ሽያጭ ላይ የሚያተኩር ነው። ድርጊቱ የተከወነው ደግሞ በዓፄ ቴዎድሮስ ዘመነ-መንግሥት።

«በዘመነ ማርቆስ በአጼ ዮሐንስ በእጨየ ቴዎፍሎስ በጸባቲ ወርቅነህ በመጋቢ መርያዊ በቄስ ገበዝ ወልደ ስላሴ፣ በሊቀ ዲያቆን ክንፈ ሚካኤል፣ በቃቤት ገብረ ማርያም በሊህ ሁሉ ሹመት ያጤ ወገኑን ቦታ ግልቱ ንጉሤ በሰባት ብር ሸጦአል። አባ ገብረ ማርያም መድኑ አድጎ እጸቱ ነው።»

ጢስ ዓባይ ፏፏቴ ባህር ዳር አቅራቢያ
በባህር ዳሩ የግእዝ ጉባኤ ላይ ተሳታፊዎቹ ሦስት ዓበይት ድምዳሜዎች ላይ መድረሳቸውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገልጠዋል። የግእዝ ቋንቋ በሀገሪቱ እየተዘጋጀ በሚገኘው የቋንቋ ፖሊሲ ላይ ይካተት የሚለው ቀዳሚው ነው። ከትምኅርት ሚንስቴር ጋር በመነጋገርም የግእዝ ቋንቋ ከአንደኛ ደረጃ አንስቶ እስከዩኒቨርሲቲ ድረስ እንደ አንድ የትምኅርት አይነት ይሰጥ የሚለው ኹለተኛው ድምዳሜ ነበር። በሦስተኛ ደረጃ ግእዝን የሚመለከት ሀገራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ወደፊት ጉባኤ እንዲከናወን የሚል ድምዳሜ ላይም ተደርሷል።

የባሕልና ቱሪዝም ሚንስቱር ድኤታ ሙሉጌታ ሠዒድ በበኩላቸው የግእዝ ዓመታዊ ጉባኤ ወደፊት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል። ቋንቋው የበለጠ ጥናት እና ምርምር እንዲደረግበት የሚመለከተው አካል ኹሉ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ጠይቀዋል።

በጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ላይ የሠፈሩት የሠነድ ምዝገባና የውል አገልግሎቶች በትክክል ከየትኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ እንደጀመረ ለማወቅ አልተቻለም። ሆኖም እንደ ዲያቆን ዳንኤል ጥናታዊ ጽሑፍ ከሆነ ጥንታውያን መጻሕፍቱ መሠል አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ሺህ ዓመታት ተቆጥሯል። 8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተፃፈ የሚታመነው የእንዳ አባ ገሪማ የወርቅ ወንጌል የንጉሥ አርማሕን የርስት ስጦታ መዝግቦታል ሲሉ ዲያቆን ዳንኤል በጥናታዊ ፅሑፋቸው አስፍረውታል።

2 comments:

  1. This is a very important issue needs to be done longtime ago, however I appreciate Deacon Daniel for all his works he has done forOrthodox Tewahedo Church. I also would like to see someone post the whole Wengiel chanting on YouTube or somewhere in order to teach ourselves. If this is already done please post the link under this article.

    ReplyDelete
  2. Ok you post my positive feedback about Geize, but you didn't like my comment about Deacon Ashenafi. Fair enough but I just want to let you know he preach Wengeil very well. I think some people are gifted to preach Wengiel and some of them are gifted to preach about Ssint Marry. I would like to see all of them balance their teaching, but I don't like when you guys judge them. However I am going to pray for Deacon Ashenafi to have his preach including Saint Marry. I may talk to him soon and give him my constructive feed back. I would like everybody including Begashaw serve Kidest Betekerstian.
    I appreciate your effort. this is not something I want you to post. I just want to send my opinion. Please have Wengel Chanting statement posted some where for self teaching by following the book.
    May God Bless All!!! Melkam Tinsaye!
    Hihit Michael

    ReplyDelete