Wednesday, April 22, 2015

ቅዱስ ሲኖዶስ ዘግናኝ ግድያ ለተፈጸመባቸው ኢትዮጵያውያን ጸሎተ ፍትሐትና ምህላ እንዲደረግላቸው ወሰነ




በሰሜን አፍሪካ ሊቢያ ውስጥ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 .. አሰቃቂና አረመኔያዊ ግድያ ለተፈጸመባቸው ኢትዮጵያውያን፣ ከሚያዝያ 14 ቀን 2007 .. ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ጸሎተ ፍትኃትና ጸሎተ ምህላ እንዲደረግላቸው፣ የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 .. ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

በሜድትራኒያን ባህር ዳርቻ አካባቢ ሁሉም የክርስትና እምነት ተከታዮች መሆናቸው በተገለጸው ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ ከምንጊዜውም በተለየ ሁኔታ እጅግ በጣም እንዳሳዘነውና እንዳሳሰበው የገለጸው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ድርጊቱ በአንድ የሃይማኖት ተከታዮች ላይ ብቻ የተፈጸመ ሳይሆን፣ በሁሉም የዓለም ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የተቃጣ የወንጀል ተግባር መሆኑን ገልጿል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የሃይማኖት ተቋማት፣ እንዲሁም የዓለም መንግሥታትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ድርጊቱን ከማወገዝና ከመቃወም ባለፈ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ፈጣንና ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ እንዳባቸው አክሏል፡፡


በእምነቱ ተከታዮች ላይ አይኤስ የተባለው የሽብር ቡድን የፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ እንደምታወግዝ፣ የአሸባሪዎች የጥፋት እልቂት ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ፆታንና አካባቢን ሳይለይ በሰው ዘር ላይ የዘመተ የጥፋት ተልዕኮ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሃይማኖትና በሌሎች ነገሮች ሳይቀር ሳይለያዩ ከጥንት ጀምሮ ጠብቀው ያቆዩት፣ በኅብረት፣ በአንድነት፣ በፍቅርና በመቻቻል የመኖር ፀጋ አጥብቆ በመያዝ፣ የጋራ ጠላት የሆነውን ግብረ ሽብር የመመከት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጿል፡፡

ልጆቻቸው በአረመኔያዊ ግፍ የተገደሉባቸው ቤተሰቦችን ያፅናናው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ልጆቻቸው በዚህች ዓለም የመኖር መብታቸው በአጭሩ ቢቀጭም፣ ‹‹የተገፉ መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ›› በተባለው አምላካዊ ቃል የወላጆቻቸውን እንባ እግዚአብሔር ያብሳል፡፡ የልጆቻቸው ሰማዕትነት በእግዚአብሔር መንግሥት ዋጋ ስላላት ወላጆቻቸው እንዲፅናኑ አሳስቧል፡፡ ሁሉም ቤተሰቦች የሟቾችን ስመ ክርስትና፣ ፎቶግራፍና ሙሉ አድራሻቸውን ለቤተክህነት እንዲልኩ ሲኖዶሱ ጠይቋል፡፡ በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከመሰል ጥቃት ለመታደግ እንዲቻል፣ ከመንግሥት ጋር በቅርበት የሚሠራ ዓቢይ ኮሚቴ በአስቸኳይ የሚያቋቁም መሆኑንም ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቋል፡፡ ከሚያዝያ 14 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2007 .. ድረስ የአርመን ክርስቲያኖችን ታላቅ ዕልቂት 100 ዓመት ዝክር ላይ ለመገኘት ሚያዝያ 11 ቀን 2007 .. ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ ሰርዘው የቀሩት ፓትርያርኩ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶችና ሌሎችም በተገኙበት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐትና ምህላ እንደሚደረግ ሲኖዶሱ በውሳኔው አሳውቋል፡፡
 SOURCE :- Reporter

No comments:

Post a Comment