Sunday, June 14, 2015

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የሰንበት ት/ቤቶች እየተወዛገቡ ነው

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን÷ ከሙስና እና ብልሹ አሠራር መንሰራፋት፣ ከመልካም  አስተዳደር እና ፍትሕ ዕጦት፣ ከአስተምህሮ እና ሥርዐት መጠበቅ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት /ቤት እና በየሰንበት /ቤቶች መካከል የተቀሰቀሰው ውዝግብ እንደቀጠለ ነው፡፡


በሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት÷ ሌቦች እየተበራከቱ፣ ጎጠኝነት እየተስፋፋ፣ በመናፍቅነታቸው የተወገዱ ግለሰቦች ተመልሰው እየተቀጠሩና አስተምህሮውን እየተፈታተኑ መሆናቸውን ሰንበት /ቤቶቹ ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ሕገ ወጥ ሰዎችን አልደግፍም›› የሚለው ሀገረ ስብከቱ በበኩሉ፤ ካህናት ሙሰኞች ናቸው  ብሎ ንደማያምን ጠቁሞ፤ ‹‹ሰዎችን ሰረቃችሁ ለማለት ማስረጃ ያስፈልጋል›› ብሏል፡፡በሀገረ ስብከቱ የሰንበት /ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የሚመሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰንበት /ቤት አባላት፣ ባለፈው ማክሰኞ ከሀገረ ስብከቱ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት ጋር በሀገረ ስብከቱ ይፈፀማል በተባለው ብልሹ አሠራር ላይ ያካሄዱት ውይይት ባለመግባባት ተቋጭቷል፡፡ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በማጋለጣቸው ‹‹የፖሊቲካ ድርጅቶች ደጋፊዎች እና ሁከት ቀስቃሾች ናቸው፤ ፓትርያርኩን ይቃወማሉ›› በሚል እየታሰሩ እንደሆነ በውይይቱ ላይ የተናገሩት የሰንበት /ቤቶቹ፤ በሰሚት መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አሠራሩን የተቃወሙ በፖሊስ ጣቢያ ታስረው ክሥ እንደተመሠረተባቸው፤ ካህናትም የንስሐ አባት እንዳይኾኗቸው በደብዳቤ መመሪያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡በሀገረ ስብከቱ ባለሥልጣናት የሚመኩና የጥቅም ትስስር ያላቸው የአድባራትና የገዳማት ሓላፊዎች ከሦስት እስከ አራት ሺሕ ብር ያልበለጠ ደመወዝ እየተከፈላቸው ውድ ዋጋ ያላቸውን መኪኖችን እንደሚነዱና ቤት እንደሚገዙ ጠቁመው ገንዘቡ ከየት እንደመጣ ሊጣራ ይገባዋል ብለዋል። ሀገረ ስብከቱ የሙዳዬ ምጽዋት ቆጠራ በካሽ ካውንተር እንዲከናወን ማድረጉን ቢደግፉም በፐርሰንት አከፋፈል፣ በቦታ እና በሕንፃ ኪራይ፣ በሠራተኞች ቅጥርና ዝውውር ረገድ በጥቅም ትስስር የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ፤ በየአጥቢያው የሚታየው የጎጠኝነት መከፋፈል መፍትሔ እንዲያገኝ አበክረው ጠይቀዋል፡፡

ሰንበት /ቤቶቹ ለዘረዘሯቸው በርካታ ችግሮች  ምላሽ የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ሰዎችን ሰረቃችሁ ለማለት ማስረጃ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ‹‹ካህናት ሙሰኞች ናቸው ብለን አናምንም፤ መኪና ቢኖራቸው ቪላ ቤት ቢኖራቸው ደስ ይለናል፡፡ ካህናት የሀብት ችግር አለባቸው እንጂ ታማኞች ናቸው›› ሲሉ ተናግረዋል፤ ከሙዳይ ምጽዋት ጥገኝነት ይልቅ በልማት ሥራ መሠማራት እንደሚመረጥም አብራርተዋል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የሠራተኛ ቅጥር እየተፈጸመ ያለው በውድድር እንደሆነና ለውጡ ባይጠናቀቅም መጀመሩ መልካም ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ በቤተ ክርስቲያን ጎጠኝነትን ጨምሮ ሙስናን በሁለንተናዊ ገጽታው መዋጋት ይገባል ብለዋል፡፡


No comments:

Post a Comment