Wednesday, June 29, 2016

በቁስላችን ላይ ጥዝጣዜ እንዳይጨመርብን



በቀሲስ ስንታየሁ አባተ
 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ከርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወርኀ ግንቦት 2008 . ባካሄደው ርክበ ካህናት በቅርቡ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም መወሰኑንና ለዚህም ዕጩዎችን የሚያቀርብ ኮሚቴ መሠየሙን በመግለጫው አሳውቋል። በርካቶች አኅጉረ ስብከት ብፁዓን ኤጲስ ቆጶሳቶቻቸውን በእርግና፣ በሕመም፣ በሞትና በመሳሰሉት ምክንያቶች በማጣታቸው ያለ አባት መቅረታቸውና አገልግሎታቸው መስተጓጎሉ ይታወቃል። ከችግሩ የተነሣም አንዳንድ ኤጲስ ቆጶሳት ሁለት ሦስት አኅጉረ ስብከት ደርበው እንዲይዙ ተደርጓል። ይህ ደግሞ በብፁዓን አባቶች ላይ የሥራ ጫናን ፈጥሯል፤ የአኅጉር ስብከት አገልግሎት የተቀላጠፈ እንዳይሆንም የበኩሉን አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

 
ዘመናችን እንደ ጥንቱ በርቀት ሆኖ በመልዕክት አገልግሎትን መፈጸም ማስፈጸም የሚቻልበት አለ መሆኑን፣ ቤተ ክርስቲያናችን ከውስጥም ከውጪም እየተደነቀረባት ካለው ፈተናም ዓይነትና ብዛት አንጻር፣ ይልቁንም ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ልትጠራቸውና አጥምቃ ልታስገባቸው ከሚጠብቋት ነፍሳት አኳያ የቅዱስ ሲኖዶሱ አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሠየም መወሰኑ ወቅቱን የዋጀ ውሳኔ ነው። ይህ መልካም ሐሳብና ውሳኔ የአባቶቻችን የተልዕኳቸው አንዱ አካልና ከክርስቶስ የተቀበሉት አደራ ቢሆንም መልካም ማሰብ በራቀበት ዘመን ይህን ስላሰቡልን ከልባችን ልናመሰግናቸው ይገባል።
 
አባቶች ድርሻቸውን ለመወጣት አንድ ርምጃ ተራምደዋል። በእነርሱ ርምጃ ልክ መከተል ደግሞ የማኅበረ ካህናቱ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና የማኅበረ ምዕመናን ድርሻ ነው። ይህ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የቀበሌ ምርጫ አይደለም። አካለ ክርስቶስ በሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ምዕመናንን የመጠበቅ፣ የመቀደስ፣ የመመገብ፣ ወደ ጽድቅ ጎዳና የመምራት፤ ከእምነት በአፍኣ የሚገኙ አሕዛብን በወንጌል መረብነት የማቅረብ፣ የማንፃት፣ የመጠበቅ ታላቅና ሰማያዊ የሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚፈጽሙ ራሳቸውን ማለት እከብር ባይ ልቡናቸውን የካዱ መንፈሳውያን መሪዎችን ለመሠየም የሚደረግ ምርጫ ነው።
ይህ ምርጫ ያለ ጥርጥር ቢያንስ ከአራት አቅጣጫዎች ከፍተኛ ፈተና ይደርስበታል ተብሎ ስጋት ፈጥሯል፤


1.      ከመንግሥታዊ ባለ ሥልጣናት
ሕገ መንግሥቱ በአስራ አንደኛው አንቀጹ መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖት በመንግሥት አንዱ በአንዱ ጣልቃ እንደማይገባ ቢደነግግም ሕጉ ከወረቀት አልፎ መሬት ሲነካ ማየት ግን የሕልም እንጀራ መሆን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ለዚህ ደግሞ ተወቃሹ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የራሳችን አባቶች ጭምር ናቸው። በቅርቡ በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቅዱስ ፓትርያርኩ መንግሥት ጣልቃ ይግባልኝ ባይነት የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን በስብሰባው ላይ መገኘታቸው ይታወቃል።

ቅዱስ ፓትርያርኩም ይጠይቁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱም ይፍቀዱ የክቡር ሚኒስትሩ በስብሰባው መገኘት ፍትሐዊ አይደለም። ቢጠየቅ እንኳን መንግሥት ጉዳያችሁን በራሳችሁ ፍቱ ብሎ ጉዳዩን ለባለ ጉዳዩ ብቻ መተው ነበረበት። ይህ ክስተት እንደ አስፈላጊነቱ መንግሥትሲያምንበትበቤተ ከርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ያሳያል። ይህን ጉድ ብለን አድንቀንም አዝነንም ሳንጨርስ ከወደ ጋምቤላ ደግሞ የባሰ ነገር ሰማን። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርየጋምቤላና የደቡብ ሱዳን አኅጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ኤጲስ ቆጶስነት ካልተሾሙ አብረን መሥራት አንችልም፤ ሌላ አባት አንቀበልም የሚል ደብዳቤ ለቅዱስነታቸው መፃፋቸውን ሰማን፤ ደብዳቤያቸውንም በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች ተለጥፎ አነበብን። እነዚህ ክስተቶች እንደ ቀድሞው ሁሉ ዛሬም መንግሥታዊ ባለ ሥልጣናት ለሥርዓተ መንግሥታቸው መጠበቅ ወይም የቅርብና የልብ ወዳጃቸውን ወደ ከፍተኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን ወንበር ለማምጣት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚሠሩ መሆናቸውን ያሳያል።
 
በመሆኑም በቅርቡ ይከናወናል ተብሎ የሚጠበቀው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ከሥርዓቱም ሆነ ከሥርዓቱ አስፈጻሚዎች ጫን ከበድ ያለ ፈተና ወይም ተፅዕኖ ይደርስበታል ተብሎ ይሰጋል።




2.       ከውሉደ ሲሞን ሲሞን
በሐዋርያት ዘመን የነበረ ጠንቋይ ነው። በክርስቶስ አመንኩ በማለት ወደ ሐዋርያት ቀርቦ ነበር። መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳን ሐዋርያት እጅ የሚያደርገውን ገቢረ ተአምራት በተመለከተ ጊዜ የቀደመ ግብሩ ማለት ጥንቆላውና በዚያ ያገኝ የነበረው ገንዘብ ትዝ አለው። በክርስትና ስም የተወውን ጥንቆላ የክርስትና ካባ አልብሶ ያጣውን ገንዘብ ለመሰብስብ አቀደ። በመሆኑም ወርቅና ብር ይዞ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ በመቅረብእኔም እንደ እናንተ እጄን በመጫን መንፈስ ቅዱስን ማሳደር እንድችል ይህን ሥልጣን ስጡኝብሎ ለመነ። በእምነትና በቅድስና እርሱ መንፈስ ቅዱስ ሲፈቅድ የሚገኘውን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በገንዘብ መግዛት ፈለገ። የሊቀ ሐዋርያነት ዓላማ አደራና ግብ በውል የተረዳው ቅዱስ ጴጥሮስአንተም ገንዘብህም አንድ ላይ ጥፉብሎ አሳፍሮታል። ከዚያን ወዲህ ሥልጣነ ክህነትን በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ምርጫ ሳይሆን እጅ መንሻ ወይም ጉቦ ከፍለው ማግኘት የሚሹ ውሉደ ሲሞን ሲባሉ ግብሩ ደግሞ ሲሞናዊ ይባላል። ይህ ግብር በዘመናችን በዓለማችን ባሉ አብያተ ክርስቲያናት እያደገ እንደመጣ ይነገራል። በእኛም ሀገር ማቆጥቆጥ መጀመሩ ይነገራል። ከማቆጥቆጥ አልፎም ደህና ገቢ ባላቸው አድባራት እልቅና ወይም ፀሐፊ ሆኖ ለመሾም እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ድረስ እጅ መንሻ (ጉቦ) መክፈል ተጀምሯል ተብሎ የሰሞኑን የአለቆች ዝውውር ተከትሎ በመወራት ላይ ነው። እውነታውን እግዚአብሔር ይወቀው። በቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ተሰማኒትና ተቀባይነት አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በስጦታ ብዛት ሕሊናቸውን ለመለጎም በአማላጅ ብዛት መውጫ መግቢያ በማሳጣት ምንጩን ራሳቸውና እግዚአብሔር የሚያውቁትን ገንዘብ እንደሲሞን በማፍሰስ ኤጲስ ቆጶስነትን ገንዘብ ለማድረግ የሚጥሩ በርካቶች ናቸው። በርግጥ በእልቅና ዘመናቸው የእግዚአብሔርን ቤት ሙዳየ ምፅዋት መገልበጥ የለመዱ ደፋሮች ከፍ ባለው የኤጲስ ቆጶስነት ሥልጣን የበለጠ እናገኛለን ብለው የቻሉትን ያህል ገንዘብ ቢያፈሱ ላይገርም ይችላል፤ ድፍረቱን ለምደውታልና ነው። በዘመናችን ገንዘብአምላክሆኖ መመለኩን ስናስተውል እነዚህ ሰዎች ዕጩዎችን መርጠው ያቀርቡ ዘንድ በተሠየመው ኮሚቴ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ምን ያህል እንደሚከብድ መገመት አያስቸግርም።
 
3.       ከሐራ ጥቃ መናፍቃን
 ሰኔ 12/2008 . በአሜሪካ የተፈጸመውንየኤጲስ ቆጶሳትምርጫ ተከትሎ በዓለም ዙርያ የሚገኙ የተሐድሶ ምንፍቅና አራማጆች ልዩ ደስታን ተጎናጽፈዋል። የዚህም ምክንያቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን በመናድና ክርስትናን እንደ ምዕራባውያኑ በተሐድሶ ስም ለመግደልና ለማጥፋት በዓላማ የሚተባበሯቸው ለዘመናትም የውስጥ አርበኛ ሆነው ሲሠሩ የነበሩትኤጲስ ቆጶስሆነው በመመረጣቸው ነው። ይህን የሐራ ጥቃዎቹን ጮቤ መርገጥ ስናይ እነዚህ ሰዎች በተመሳሳይ መልኩ በሀገር ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታ ለመፍጠር ምን ያህል በዓላማ ሊሠሩ እንደሚሠሩ መገመት አይከብድም። ከአጥቢያ እስከ መንበረ ፓትርያርክ /ቤት አላቸው ተብሎ የሚነገርለትን ሰንሰለታቸውን ስናጤነው ደግሞ ስጋታችን ያይላል። ስጋታችንም አንድ ሁለት ሰው አሾልከው ያሾማሉ በማለት ብቻ አይደለም። ራሳቸውን ወደ ኤጲስ ቆጶስነት ማዕረግ ካስጠጉ ወደፊት ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን አደጋ በማሰብ እንጂ። ከዚህም በተጨማሪም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት የሃይማኖት ሕፀፅ፣ የምግባር ጉዳለት አለባቸው ብለው ለዘመናት አቤቱታ ሲያቀርቡባቸው የኖሩት መነኮሳት ለኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ጥቆማ ውስጥ መግባታቸው ራሱ የሐራ ጥቃዎች ድፍረት ምን ድረስ እየሄደ እንደሆነ ያሳያል።
 
4. ከጎጠኝነት፣ ከወንዘኝነትና ከዘረኝነት መንፈስ
የጥንት አባቶቻችን አንድን ሰው የሚያውቁት በእምነቱ ጽናትና በምግባሩ ቀናነት ነበር። ለአንድ ኀላፊነት ወይም ለሢመት ሲያጩትም መስፈርታቸው እምነቱ፣ ሥነ ምግባሩና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ጠንቅቆ ማወቅ የሚሉ ናቸው። ከዚህ ውጪ ብሔሩ፣ ቋንቋው፣ መንደሩና ወንዙ የመሳሰሉት ከግምት ውስጥ ፈጽመው አይገቡም ነበር። ለዚህም አስረጂ የሚሆነን በመልክ፣ በባሕል፣ በቋንቋ፣ በመልከዓ ምድር ከማይመስሉን ሀገር ወደኛ መጥተው ቤተ ክርስቲያናችንን ሲያገለግሉ የነበሩ አባቶችን ማንሣቱ ብቻ ይበቃናል። ከሣቴ ብርሃን አባ ሰላማ፣ ዕጨጌ ዕንባቆም፣ ተሠአቱ ቅዱሳን በትውልድ ኢትዮጵያውያን አይደሉም። በእምነታቸው ኦርቶዶክሳዊነት፣ በምግባራቸው ቅናነት ተቀብለናቸው ቅድስናቸውን ለዘመናት በማወጅ ላይ እንገኛለን።
አሁን አሁን ግን ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ወርቃማ መለያ የሆነው ገጽታ በመቀየር ላይ ይገኛል። አንድ አገልጋይ እምነቱና ምግባሩ እንዲሁም ትምህርቱ ሳይሆን የትውልድ ቀዬው ቋንቋው ነው የሚጠየቀው። ይህ መጥፎ የሆነና የነቀዘ አመለካከት በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫውም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል ተብሎ በብዙዎች ተሰግቷል። ይህም ስጋት ከባዶ ሜዳ የመጣ አይደለም። በየገዳማቱ፣ በየአድባራቱ በወረዳ ቤተ ክህነትና በሀገረ ስብከት እንዲሁም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ለሚወጡ ክፍት የሥራ ቦታዎች በሚደረጉት ውድድሮች አሸናፊ ለመሆን ዋና መስፈርቱ የሥራ መደቡ የሚጠይቀው ሙያዊ ብቃትና ተገቢው የሥራ ልምድ ሳይሆን የኀላፊው “የሀገር ልጅ” እየሆነ ከመጣ ሰንበትበት ብሏል።
የኤጲስ ቆጶሳቱን ምርጫ በተመለከተ ያነጋገርኳቸው አንዳንድ ሰዎች ከሌሎቹ ስጋቶች ሁሉ ይኸኛው እጅግ ከበድ እንደሚል ይናገራሉ። ለዚህም ዋና ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት “በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ስብሰባዎች የሚነሡ የሐሳብ ልዩነቶችን በአምክንዮአዊና በተጠየቃዊ መልኩ ከማሳመን ይልቅ በደጋፊ (ቲፎዞ) ብዛት ለማሳመን ወይም ተፅዕኖ መፍጠር የሚል እንግዳ አሠራር በአንዳንድ አባቶች ሳይቀር እያቆጠቆጠ መጥቷልና ነው” ይላሉ።
ከላይ ለመጠቆም የሞከርኳቸውና ሌሎች ያልዳሰስኳቸው ነጥቦች በቅርቡ የሚካሄደውን የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ አስምራጭ ኮሚቴዎቹን ከፍተኛ ውዝግብና ተፅዕኖ ውስጥ ሊያስገቡ ይችላሉ።
በዚህም የተነሣ ለአስመራጭ ኮሚቴነት የተመረጡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፦
1. ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ
2. ብፁዕ አቡነ ገሪማ
3. ብፁዕ አቡነ ገብርኤል
4. ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ
5. ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
6. ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ
7. ብፁዕ አቡነ አብርሃም
8. የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ተፅዕኖውን ተቋቁመው ቤተ ከርስቲያናችንን ወደ ቀደመ ልዕልናዋ ሊመልሷት ወይም በሰውም ሆነ በእግዚአብሔርም ዘንድ ሊያስጠይቃቸው በሚችል ሁኔታ በተፅዕኖው ሊደናቀፉ ይችሉ ይሆናል።
ምን እናድርግ?
ችግሮችን ብናወራ ለቤተ ክርስቲያናችን አይበጃትም። የተጠበቀው ሢመት የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት በጠበቀ መልኩ እንዲፈጸም በሰከነ አዕምሮ ልናስብና ፍጹም መንፈሳዊ በሆነ አካሄድ የድርሻችንን መወጣት አለብን። ለዚህም በሀገር ውስጥ ያሉ መላው ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምዕመናን ይልቁንም የቤተ ክርስቲያናችን ፈርጦች የሆኑ የሰንበት ተማሪዎች በውጪም ያሉት አገልጋዮችና ምዕመናን ካሁኑ መሠረታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅብናል። ከእንቅስቃሴዎቹም የተወሰኑትን ለመጠቆም ያህል፦
1. እግዚአብሔር በቤቱ የራሱን ሰዎች እንዲያስቀመጥ አብዝቶ መጸለይ
በጸሎት የማይደረግልን ነገር የለም። ይልቁንም ስለ ቤቱ በቀናነት የምናቀርበውን ልመና እግዚአብሔር ይሰማል። ይለማነናል። ከጥላቻ፣ ከሕሜት፣ ከቡድናዊ ስሜት ርቀን የራሳችንን ሃሳብ ወደ ጎን ትተን በሙሉ እምነት እንጸልይ። ይልቁንም ከፊታችን ታላቁና ተወዳጁ የፍልሰታ ጾም እየተቃረበ ስለ ሆነ በጾማችን ወቅት በእመቤታችን አማላጅነት ወደ እግዚአብሔር ከምናቀርበው ልመና አንዱና ተቀዳሚው የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ይሁን። በሥራና በጤና ምክንያት ይህን ማድረግ የማንችል ደግሞ መብዓውን ወደ ገዳማቱ እንላክና አባቶች እንዲጸልዩበት እናድርግ። ከወዲሁም በየገዳማቱ ያሉ አባቶች ጉዳዩን ተረድተው አጥብቀው እንዲጸልዩ አደራ እንበላቸው።
2. መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችል መረብ መፍጠር
ቤተ ክርስቲያናችን ዓለም አቀፋዊት እንደመሆንዋ አገልጋዮቿ በመላው ዓለም ተሰራጭተው ይገኛሉ። የሚመረጡትም ከነዚሁ በመላው ዓለም ተሰራጭተው ካሉት አገልጋዮቿ መካከል ነው። ስለዚህ ተኩላ ከበጎች ጋር ተመሳስሎ እንዳይገባ በዕጩነት ስለሚጠቆሙት ፍጹም የቤተ ክርስቲያን አባትነት መረጃ መለዋወጥ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የመረጃ መረብ ሊኖረን ይገባናል። በመሆኑም ሙያውና ለቤተ ክርስቲያን መቆርቆሩ ያላችሁ ወገኖች ጊዜ ሳትሰጡ አስቡበት። የመረጃ መረቡ የቤተ ክርስቲያናችንን ሕልውና ከነሙሉ ክብሯ ከማስጠበቅ ውጪ አንዳች ፖለቲካዊ አጀንዳ እንዳይኖረው አዘጋጆች ልዩ ጥንቃቄ አድርጉልን። ይህ አንድነታችንን ያላላዋል እንጂ አያጠብቀውም።
3. በሚደረጉ ውይይቶች በንቃትና በትጋት መሳተፍ
ለዕጩነት በሚቀርቡ አባቶች የእምነትና የሥነ ምግባር ብቃት ላይ በነበሩባቸው አድባራትና ገዳማት ባሉ ካህናት፣ ምዕመናንና የሰንበት ተማሪዎች ውይይት እንደሚካሄድ ተነግሯል። በዚሁ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሳችን በመግለጫው ያሰማንን ቃል እንዲያከብር መጠየቅ፣ ለውይይቱ መድረክ ከተከፈተም በፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ጨዋነት ልንሳተፍ ይግባናል።
መጥፎ ባሕል ሆኖብን ለውይይት ዕድሉ ሲሰጠን መናገር የማይሆንልን ከመድረክ ስንወርድ ማጉረምረምና ማማት የምንወድ ብዙዎች ነን። ይህ እንኳን ለቤተ ክርስቲያን ለጉርብትናም አይበጅም። ካለፈ በኋላ ተኩላው ከበግ ጋር ተመሳስሎ ገብቶ “ይድልዎ” ተብሎ ከተሠየመ በኋላ መጮሁ አይጠቅምም።
4. እንቅስቃሴዎችን በንቃት መከታተል
ቅዱስ ሲኖዶሱ የኤጲስ ቆጶሳቱ ምርጫ አጥቢያ ድረስ ወርዶ ውይይት ይደረግበታል ብሎ መወሰኑ ያስደሰተን የመኖራችንን ያህል ያሳዘናቸው አሉ። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ዓላማ አድርገው የተነሡት ነገር በውይይት የሚከሽፍባቸው መስሎ ከታያችው የተለያይ የማዘናጊያ ዘዴዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ለዘመናት የሰንበት ተማሪዎችን እንደ ጠላት በማየት አላሠራ ያላሉትን ያህል አሁን ከእነርሱ ድጋፍ ለማግኘት አዳራሽ እንዲሠራላቸው፣ አዲስ የደንብ ልብስ እንዲሰፋላቸው፣ የጉዞ መርሃ ግብሮች በሰንበት ትምህርት ቤት ብቻ እንዲካሄዱ፣ ካሀናት ደመወዝ እንዲጨመርላቸው፣ ቀድሞ ነጋ ለኪዳን መሸ ለቁርባን አልተገኘህም ብለው ደመወዝ ይቆርጡ የነበሩት አሁን እጅግ ትኁት ሆነው የካህናቱንና የሰበካ ጉባኤ አባላቱን ጉልበት ለመሳም የሚዳዳቸው፣ የተረሳውን የልማት ዕቅድ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ ደፋ ቀና ማለት የጀመሩ እንዳሉ በስፋት መታየት ጀምሯል።
ከዚሁ በተጨማሪም በውይይቱ ላይ መላው ማኅበረ ካህናቱና መላው የሰንበት ተማሪዎች እንዳይሳተፉ የቦታ፣ የሰዓት ጥበትን፣ የጥበቃና የደኅነንት ጉዳይን በማንሣት የተወሰኑት ብቻ እንዲሳተፉ በሚል ሽፋን ባዘጋጇቸው ቡድኖቻቸው መልካምነታቸው ብቻ እንዲወራላቸው እስከማስደረግ ሊሄዱ ይችላሉ። ግፋ ሲልም በብርቱ ይቃወሙናል የሚሏቸውን የሰንበት ተማሪዎች በሰበብ ባስባቡ በውይይቱ ዕለት ሊያሳስሩ ይችሉ ይሆናል። ስለዚህ ካህናቱ ምዕመናኑና የሰንበት ተማሪው በንቃት ሊቀድማቸው ይገባል። “ዝምታ ለበግም አልበጃት፤ አሥር ሆና ወጥታ አንድ ቀበሮ ፈጃት” ነው የሚባለው?
5. መረጃዎች ለአስመራጭ ኮሚቴው ማድረስ
በእጃችን ያሉ ወይም ከተለያዩ ቦታዎች የምናገኛቸውን መረጃዎች ፎቶ ኮፒ እያነሣን ለአስመራጭ ኮሚቴው ብናደርስ የተጠቋሚዎችን ማንነት መላልሰው እንዲያጤኑት የሕዝቡንም ድምፅ እንዲሰሙ ያደርጋል። በርግጥ ባልተጣራ መረጃ ራሳችንን ወደ ስሕተት እንዳናስገባ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ንጹሑንና ኦርቶዶክሳዊውን አይገባውም፤ ነቀፋ ያለበትን ደግሞ ይገባዋል ብሎ ማቅረብ “በሐሰት አትመስክር” ያለውን የእግዚአብሔር ቃል መተላለፍ ነው። ይህ ደግሞ ማንንም ይሁን በፍርድ ቀን ያስጠይቃል። ስለዚህ መረጃዎቻችን እውነተኛ መሆናቸውን እንመርምር፤ ለአባቶቻችን እናድርሳቸው።
6. ከቡድናዊ ስሜት መውጣት
የተጠመቅነው ከምድራዊ ቡድናዊነት ወጥተን ወገንተኝነታችን ለእግዚአብሔርና ለመንግሥቱ ብቻ እንዲሆን ነው። አባ እገሌን ልናውቃቸው ልንቀርባቸው እንችላለን። ከእርሳቸው በፊት ግን በአርባና በሰማንያ ቀናችን ያወቅነው ቤተ ክርስቲያንን ነው፤ እግዚአብሔርን ነው። ዲያቆናቱን፣ ቀሳውስቱን፣ ጳጳሳቱን ያስገኘች ቤተ ክርስቲያን ናት። ራሷና ጉልላቷ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ ቡድናዊነታችን የመድኀኒታችንን ፈቃድ ከመፈጸም ጋር ነው መሆን ያለበት። እምነታችን የወንዝ፣ የጎጥ፣ የቋንቋና የፖለቲካ ዘረኝነትን ካላሸነፈ ገና ክርስቶስን ባለማወቅ በድንቁርና ጫካ ውስጥ ነው ያለነው።

አንድ ነገር እናስብ። በቤተ ክርስቲያን ላይ ቀርቶ በአንድ ግለሰብ ላይ የሚደረገውን ደባ አምላካችን በደብረ ጽዮን በክብር ሲገለጥ ሁሉን ይፋ ያደርገዋል። ዋጋውን እንደሥራውም ይከፍለዋል። ስለዚህ ክርስቶስ በደሙ ይቀድሳትና ያነፃት ዘንድ በመስቀል ላይ የዋለላትን ቅድስት ቤተ ከርስቲያን ከከበቧት የበግ ለምድ ከለበሱ ተኩላዎች እንጠብቃት። እግዚአብሔር ሆይ ቤተ ክርስቲያንህን አስብ። አሜን።

1 comment: