Saturday, July 1, 2017

ኑፋቄ የማይሰለቻቸው ቅብጥብጡ ሐራጥቃ

"ኢየሱስ ክርስቶስ ማለት አማላጅም ነው ተማላጅም ነው" ወልደ ትንሣኤ አያልነህ
  

የሰውየን ነገር ከዚህ ቀደም "ጵጵስና" አይገባውም በሚል ሀሳባችንን ለመግለጥ ሞክረናል፡፡ ዲያቆን ኤፍሬም እሸቴ "ኢይደልዎ" በሚል ያቀረበውን ጦማርም ኾነ ሌሎች ብዙዎች ተቆርቋሪዎች ድምጻቸውን ማሰማታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ በእነዚያ ምጥን ጦማሮች መነሻነት የተብሰከሰኩ ሁሉ ስሜታቸውን መግለጣቸው ይታወቃል፡፡

እንዲህ ሲለይለት ጥሩ ነውና እዚያም እዚህም ያለነው ቁርጣችንን ዐውቀን መንገዳችን እንዳይንጋደድ ይረዳናል፡፡ ለመወሠንም ጊዜው አሁን ነው፡፡ በውዥንብር የቆዩ ብዙ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሰውየው በገባ ወጣ ጨዋታ ስልት የተካኑ ስለነበሩ ብዙዎችን ሲያጭበረብሩ ኖረዋል፡፡ ድሮም ቢኾን በማንኪያ ሲፋጅ ሲበርድ በእጅ እያሉ ሲያምታቱ ቆዩ እንጂ ለማዕዱ ክብር የበቁ አልነበሩም፡፡ ያዳቆነ . . . እንዲሉ የኑፋቄውን ጫፍ እስኪነኩት ድረስ አቻኩሎ እዚህ አደረሳቸው፡፡ ምእመናን በዚህ ሊሸበሩ አይገባም፡፡ በተለይ ዝናን ተከትሎ የሚመጣውን ቅስፈት ማንም አይችለውምና እያሳበደ ከምእመናን በረት አስወጣቸው፡፡ ወደ ውጭ ከማየት ወደ ውስጥ ወደ መመልከት ማዘንበል ያስፈልጋል፡፡ ስለፈቃድ እብደት ሲናገሩ ከራርመው ራሳቸው በፈቃዳቸው አብደው አረፉት፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ጽኑ በሽታ ይነቅልላቸው ዘንድ ምኞታችን ቢኾንም ኑፋቄያቸውን ግን አንታገሠውም፡፡


ተከድኖ የኖረው ኑፋቄ አሁን ተገለጠ፡፡ ዳር ዳሩን ሲዞሩት ኖረው ኖረው አሁን ወደ መኻሉ ገቡ፡፡ አስከዛሬ ዋነኛ ሥራቸው የነበረው ድንበር ማፍለሱ ላይ ነበር፡፡ በኦርጋን ስለመዝፈን፣ ቁንጫ እና አሳማን ስለመሳሰሉ አዝማደ መባልዕት፣ በጫማ ወደ መቅደስ ስለመግባት እንዲህ እና እንዲያ እያሉ ሲቀዛፍቱ የኖሩት በእኛ እና በፕሮቴስታንቱ መካከል ያለውን ድንበር ለማፍለስ ነበረ፡፡ ተስፋ ቆረጡ እና ወደ መሠረታዊው ክህደት ራሳቸውን ወግተው ጣሉ፡፡

"ስምዐ ተዋሕዶ" በሚል ባሳተሙት መጽሐፍ ድፍረታቸውን ሲገልጡ ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጠይቀው መልስ እንዳላገኙ መናገር ይጀምራሉ፡፡ ለእርሳቸው ትርኪ ምርኪ ጥያቄ ከጎንደር ሊቃውንት መካከል የሚመልስላቸው አጥተው በመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ኰኵሐ ሃይማኖት ነፍሳቸውን እንዳተረፉ ይነግሩናል፡፡ በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን ለማግኘት ሸዋ ድረስ መምጣት እንዳስፈለጋቸው ሲገልጡ "ነፍሳቸውን ይማርና" በማለት የድፍረት ቃል ይናገራሉ፡፡ መንፈሳዊ አባትን ቀና ብሎ "ነፍስ ይማር" ማለት የድፍረት ድፍረት ነው፡፡ በረከታቸው ይደርብንና ማለት ሲገባ እንደ ማንም ተራ ምዕመን በማይባለው መጥራት የክህደታቸው መገለጫ ነበረ፡፡ መጽሐፉም ርእስ እንጂ ንባብ የለውም፡፡ እንደ ገለባ ክምር በታትኖ ለሚመለከተው ከገለባ በስተቀር ግርድም አይገኝበት፡፡ ያንኑ ነገረ ቁንጫቸውን ለማለባበስ የከመሩት ባዶ ቁልል ነው፡፡ ስምዐ ተዋሕዶ የሚለው ቃል ግን ክቡድ እና እንደ አርሳቸው ያለ እምነቱ የቀለለ ሊጠቅሰው የማይገባ ነው፡፡ ራስ ከብዶ ዕውቀት ባዶ ይባላል፡፡

ለዶግማ ቦታ የሰጡ ይመስል በመግቢያው ላይ "ለቀኖና እና ለባህል ምዕራፍና ቁጥር ብየ መረጃ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን ስቆፍር አባቶቼንም መልሱን ውለዱ እያልሁ የኖርሁበትን ዘመን ሳስብ እጅግ ይገርመኛል" በማለት በፀፀት ይንገበገባሉ፡፡ ነገሩን በማራዘምም "ሃይማኖት ነው ብላችሁ በሥርዓቱ ድነናል ትላላችሁ ብለው ሲጠይቁን የምንመልሰው ስለሌለን፤ ልጆቻችንም አብዛኛውን ጊዜ የሚመልሱት ስለሌላቸው፣ እኛንም ሲጠይቁ አንድ አንድ ጊዜ ተገቢውን መልስ ስለማንሰጥ ልጆቻችን ሃይማኖታችን ውሸት እየመሰላቸው እየተውት ለሌላው ሲሳይ ኾነዋል" ይላሉ፡፡ ገጽ ፳፫ እና ፳፬፡፡
ራሳቸው ስለቀኖና ሲጽፉ የማይታለፍ ቢኾንባቸው የመጀመሪያውን የቅዱሳን ሐዋርያት ድንጋጌ ያነሣሉ፡፡ ከቅዱሳን ሐዋርያት ውሣኔ አንዱ "ከዝሙት ራቁ" የሚል ነው፡፡ ሥራ ፲፭፥፳፰። ከዝሙት መራቅ ዶግማ ነው ቀኖና? ከዐሥርቱ ትእዛዛት አንዱ እርሱ አይደለምን? ውሣኔው ደግሞ የሲኖዶስ ተሰብሳቢዎች የኾኑት ብቻ ሳይኾን የመንፈስ ቅዱስም እንደኾነ ሲያጠይቅ "እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል" በማለቱ ይታወቃል፡፡ ያነበቡት ኧረ እንደ እርሳቸውስ የቆፈሩት መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አላሳያቸውምን? ለበለዓም ያልታየው መልአክ ለአህያዋ መታየቱን ልብ እናድርግ፡፡ በለዓምን መልአክ የለም ቢል ማን ይሰማዋል? ወልደ ትንሣኤ አያልነህም ቁጭታቸው ለምን ንባቡ እያለ አልተነበበልኝም ነው እንጂ ንባቡስ ነበረ። ለዚህ ደግሞ ራስን እንጂ ሌላ ለማማት አያደርስም፡፡

በመጽሐፋቸው የሲኖዶስ ውሣኔ ሁሉ ሊሻሻል ይችላል የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡ ቀኑ ሲገጥምላቸው በሲኖዶስ አባልነት ሰበብ ብቅ ሊያደርጉት ያሰቡትን ጉዳይ ከወዲሁ ይጠቁማል፡፡ ቀኖና ሁሉ ይሻሻላል ብለው ከተነሡ ከቅዱሳን ሐዋርያት ድንጋጌ አንዱ "ከዝሙት ራቁ" የሚለውን ወደየት ሊያሻሽሉት ይፈልጋሉ? ቀኖና ሲባል በመደዳ ማሻሻል ይቻላል ማለት ዶግማን እስካልነካ ድረስ እንጂ በጉባኤ ሲኖዶስ የተወሠነውን ሁሉ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንዳልተገኘበት ሁሉ ፍርስርሱን ለማውጣት ጥርጊያውን መጀመሩ ለካ እዚህ ለመድረስ ነበረ፡፡

አዲሱ ፍጹም ክህደታቸው (አዲስ ማለት በገሃድ የተነገረውን እንጂ የውስጡማ የቆየ ለመኾኑ የተረገዘው በመወለዱ ታወቀ) ላይ ለመድረስ የመጠበቂያ ግንቦችን ማፈራረስ እንደነበረባቸው አስበው ነበር፡፡ እንዳሰቡት ጥርጊያውን ሳይሠሩት መንገዱ ጠፋባቸው እና ራሳቸውም ጠፉ፡፡ ሲገነፍልባቸውም "ኢየሱስ ክርስቶስ ማለት አማላጅም ነው ተማላጅም ነው" ብለው አረፉት፡፡

አማላጅነት እና አስታራቂነት ምን እና ምን ናቸው?
አማላጅነት
አማላጅነት በጸጋ እግዚአብሔር የሚገኝ የቅድስና ውጤት ሲኾን ሰጪው እግዚአብሔር ነው፡፡ በምናውቀው ዓለም አማላጅ ተላከ ማለት ወድቆ ተነሥቶ፣ ለምኖ ለማስማማት ወይም ለማግባባት የሚደረግ ሲኾን የአንዱ ወገን በዳይነትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የበደለው ሰው ወደተበዳዩ አማላጆችን ሲልክ በደሉን አምኖ ይቅርታ ለመጠየቅ ሰውነቱን አዘጋጅቶ ልቡ ፈቅዶ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ ተማላጁ መበደሉ (ተበዳይነት) አማላጅ ላኪው ማጥፋቱ (በዳይ መኾኑ) ታውቆ ይደረጋል፡፡ በምድራዊው ሥርዓት አማላጁ ከተማላጁ በማንኛውም መስፈርት ከፍም ዝቅም ሊል ይችላል፡፡ በመንግሥተ እግዚአብሔር ግን ተማላጁ ምን ጊዜም እግዚአብሔር ሲኾን አማላጁ ፍጡር ነው፡፡ ስለኾነም አማላጆቻችን ወይ በልመና ወይ በቃል ኪዳን እግዚአብሔርን ይማጸኑታል፡፡

በቃል ኪዳን ለአባቶቻችን ወይም ለጻድቁ እንዲህ ብለህ የገባኸውን አስብ እየተባለ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ስም ይለመናል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ "ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ" ብሎ እንደማለደ፡፡ ዘጸ ፴፪፥፲፫።

       "ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም አስብ፤ የዚህን ሕዝብ ደንዳናነት ክፋቱንም ኃጢአቱንም አትመልከት" ዘዳ
       ፱፥፳፯።
       "እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፥ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን

       አሰበ" ዘጸ ፪፥፳፬።
       "ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ" ሉቃ ፩፣፸፫።


እግዚአብሔር ለቅዱሳን በገባላቸው ቃል ኪዳን እንደሚለመነው ሁሉ እንደዚሁም ደግሞ በቀጥታ ቅዱሳን በሚያቀርቡት ምልጃ ይለመናል፡፡ በዚህም ሥርዓት ፍጡራን አማላጅ ሲኾኑ እግዚአብሔር ተማላጅ ነው፡፡ እመቤታችን በቃና ያደረገችው ምልጃ የዚህ ቀጥተኛ ምሳሌ ነው፡፡ ዮሐ ፪፥፩-፲፩። ነቢያቱ፣ ቅዱሳኑ፣ መልእክቱ በቅድመ እግዚአብሔር ደጋግመው ያቀረቡት ልመና እና ያገኙት ምላሽ የዚህ ሥርዓት አካል ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ እያሉት ወርዶ አማላጅ የሚኾንበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ እግዚአብሔር የለመኑትን እንዲያደርግላቸው ደጅ ይጠኑታል፣ በአካለ ሥጋ ያሉት ይጾማሉ፣ ይጸልያሉ፣ ይሰግዳሉ በአካላ ነፍስ ሉት ደግሞ ቃል ኪዳናቸውን ያሳስባሉ፣ ልመና ያቀርባሉ፡፡

አስታራቂነት
አስታሪቂነትን ስንመለከት ግን ከዚያ የተለየ ነው፡፡ በዚህ ዓለም የሚያስታርቅ ሽማግሌ የሚባል ስም ይሰጠዋል፡፡ ሽማግሌ ወይም አስታራቂ የኾነ በሀሳብም ይሁን በጠብ የተለያዩ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ አካላትን የማቀራረብ ሥራ ይሠራል፡፡ በሀሳብ ይሞግታል፡፡ ዝቅተኝንት የለበትም፡፡ ያስማማል እንጂ አይለምንም፡፡ ዝቅ ባይነት፣ ተዋራጅነት፣ ተለማማጭነት በአስታራቂ ሽማግሎች ዘንድ የለም፡፡ እንዲያውም በታራቂዎች ዘንድ የተከበረ ነው፡፡

ስለኾነም አስታራቂነት እና አማላጅነት ለየቅል ናቸው፡፡ ቅዱሳንን አማላጅ ስንላቸው ጌታችን በመስቀል ላይ ከፈጸማቸው የቤዛነት ሥራዎች አንዱን አስታራቂነት እንለዋለን፡፡ በዚህም የተነሣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ይላሉ፡-
"የኾነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኾኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ" ፪ቆሮ ፭፥፲፰-፲፱። "እግዚአብሔር በክርስቶስ ኾኖ" ማለቱን ልብ እናድርግ፡፡ አብና መንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ ወልድ ህልው ኾነው ዓለሙን ከራሳቸው ጋር ማስታረቃቸውን ይናገራል ሐዋርያው፡፡ ክርስቶስ አስታረቀ ስንልም ብቻውን ነበረ እንዳንል አብ መንፈስ ቅዱስም እርቁ ሲፈጸም በወልድ ህልዋን እንደነበሩ ነገረን፡፡ ማስታረቅ አማላጅነት ነው እንዳንል እግዚአብሔር አብም በክርስቶስ ህልው ኾኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበር ተብሏልና እርሱንም አማላጅ ሳንለው ላንመለስ ነው፡፡
"እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና። እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ።" ቆላ ፩፥፲፱-፳፪።
ቅዱስ ጳውሎስ "በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና" ማለቱ ምንን ሲያመለክት ነው? እርቁ የተፈጸመው በሰማይ ላሉ ለመላእክት በምድርም ላሉ ለሰው ልጆች እና ራሱ ከተባለው ከጌታችን ጋር ነው፡፡ እግዚአብሔር የተባለ አብ ሲኾን ታራቂ ኾኖ የተነገረው ደግሞ ወልድ ነው፡፡ ታራቂው ወልድ መኾኑን በምን እናውቃለን ከተባለም "በመስቀሉ ደም" በመባሉ እናውቃለን፡፡ ከሦስቱ አካላት በመስቀሉ ላይ ኾኖ አርቁን የፈጸመው ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፡፡ ጌታችን እርቁን በመስቀል ላይ ሲፈጽም በእርሱ ዘንድ ህልዋን የኾኑት አብና መንፈስ ቅዱስም ጊዜ ሳይሹ አብረው ታርቀውናል፡፡ ቀድሞ ብቻውን ጌታችን ታርቆ ከዚያ በኋላ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያስታረቀ እንዳይመስለን፡፡ አንድ ጊዜ በአንድ ላይ እንጂ መቅደም መቀዳደም የለም፡፡
በዚህም ምክንያት ራሱ መሥዋዕት ኾኖ እንደቀረበ፣ መሥዋዕት አቅራቢውም ራሱ ሲኾን፣ መሥዋዕት ተቀባይም እርሱ ራሱ ነው እንላለን፡፡ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መሥዋዕት ይቀበላል፤ በዚያ ደግሞ መሥዋዕት ኾኖ ይቀርባል፣ በሊቀ ካሕንነቱ ደግሞ መሥዋዕት ያቀርባል፡፡ ሦስቱንም መኾን የቻለ እርሱ ብቻ ነው፡፡ የመሥዋዕቱ በግ እርሱ በመኾኑ ልዩ ነው፤ መሥዋዕቱም መለኮት የተዋሐደው ነፍስ የተለየው ነው፡፡ መሥዋዕቱን ያቀረበውም ሊቀ ካሕን በመለኮታዊ ሥልጣኑ፣ በሥግው ቃልነቱ እንጂ በሰውነቱ ብቻ አይደለም፡፡ በሰውነቱ ብቻማ ቢኾን ክሕነቱ የዘለዓለም ነው ባልተባለ ነበር፡፡ "አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘለዓለም ካሕን ነህ" እንዲል፡፡ ዕብ ፭፥፮።
ሐዋርያው ጌታችን እንዴት እርቅን እንደመሠረተ ሲናገር "ጥልን በመስቀሉ ገደለ" ይላል፡፡ ኤፌ ፪፥፲፮። ጥል የተገደለው በእግዚአብሔር ወልድ ሥልጣን መኾኑን እንመለከታለን፡፡ እየሞተ የሚገድል እርሱ ብቻ ነውና፡፡ መዋቲውም ጥል ነው፡፡ ጥል ከሞተ እርቅ ቦታውን መያዙ ቅጽበታዊ ነው፡፡ እነማን ታረቁ ሲባል የሰው ልጆች ከእግዚአብሔርና ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ታረቁ እንላለን፡፡ መላእክቱ የተጣሉን አምላካቸው እግዚአብሔር ስለተጣላን ነው፡፡ እርቁ የተጀመረው በማኅፀን ሲኾን በልደቱ የተዘመረው መዝሙር ያንን ያመለክታል፡፡ "ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ" እያሉ ሠራዊተ መላእክት ከእረኞች ጋር ዘምረዋል፡፡ ሉቃ ፪፥፲፬። አብረው ማመስገናቸው የመታረቃቸው መገለጫ ነው፡፡ ይህ እርቅ ሲፈጸም ልመና እንዳልሰማን ልብ እንበል፡፡
ታራቂም አስታራቂም የእርቁ መሥዋዕትም ኾኖ ሥግው ቃል ተገልጧልና እርሱ ይህን ሁሉ አደረገ፡፡ እዚህ ውስጥ አማላጅነት የለም፡፡ ሳይለምን መታረቅ፣ ማስታረቅ እየቻለ፤ ክሒሉንም አድርጎ እያሳየ በግድ ለምን ለማኝ ወይም አማላጅ እንዲባል ይፈለጋል?
ድኅነታችን በምልጃ የተመሠረተ አይደለም
በሕገ ልቡናም በሕገ ኦሪትም መድኃኒት እንጂ አማላጅ መች ጠፍቶ ያውቅ ነበር፡፡ በዘመኑ የተነሡ ቅዱሳን ሁሉ ሲያማልዱ ኖረዋል፡፡ በምልጃ ድኅነት የማይኾን ስለኾነ ነውር የሌለበት በባሕርይው ንጹሕ የኾነ አማናዊ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን ተዋሕዶ መጣ፡፡ እርሱም በሥልጣኑ ከሰው ልጆች ላይ ተጭኖ የነበረውን የኃጢአት ቀንበር አስወገደ፡፡ ኃጢአታችንን ወይም በደላችንን ተሸከመና ከእኛ አስወገደልን፡፡ ተሸከመ ሲባል የእኛ ኃጢአት ወደ እርሱ ሔደ ማለት አይደለም፡፡ ስለእኛ በደለኛ ተባለ፣ ስለ እኛ ኃጢአተኛ ተባለ ማለት እንጂ፡፡ ኃጢአት ወደእርሱ ይጠጋ ዘንድ ከቶውኑ አይችልምና የእኛን ኃጢአት ወሰደ፣ ተቀበለ ብሎ ማሰብ አይገባም፡፡ "አባ" ነኝ ባዩ ግን "የእኔን መርገም የእኔን ኃጢአት ወስዷል" በማለት ባልተገራ ቃል፣ ባልተገረዘ አንደበት እንዳመጣላቸው ይናገራሉ፡፡
መሠረተ ድኅነት በምልጃ የሚፈጸም ቢኾን ኖሮ የጌታ መሥዋዕት መኾን ባላስፈለገ ነበር፡፡ ይህንን መሥዋዕት በቅድመ እግዚአብሔር ማቅረብ የሚችል ብቁ ካሕን ስለሌለ ራሱ ሊቀ ካሕናት ኾኖ ተቀባይም አቀባይም ኾነ፡፡ እንዲህ ኾኖ መገለጡ ግን ተዋራጅነት አለበት አያሰኘውም፡፡ ስለኾነም ለቅጽበትም እንኳ ጌታችን አማለደ ተብሎ ሊነገር አይችልም፡፡ ድኅነቱ አማላጅ ሳይኾን መድኃኒት የሚሻ ነበርና ጌታችን መድኃኒት ኾኖ በሽታውን ጠራርጎ አስወገደልን፡፡ የኃጢአትን ሥር ነቅሎ የጣለውን ለምን አማላጅ ይሉታል? ቀራንዮ ላይ የተፈለገው መድኃኒቱ ነበርና እርሱ ሥጋውን ቆርሶ ደሙንም አፍስሶ እውነተኛው መሥዋዕት ኾኖ የዕዳ ደብዳቤያችንን ቀደደው፡፡ መድኃኒቱን ክርስቶስ ትቶ አማላጅ የኾነ ክርስቶስ መፈለግ ጌታችንን ከመለኮታዊ ሥልጣኑ ለማውረድ የሚሞከር የመንግሥት ግልበጣ ይመስላል፡፡
አማላጅነት የቅዱሳን ሥራ ነው፡፡ በጸጋ እግዚአብሔር የበለጸጉ ቅዱሳን (በአጸደ ሥጋም በአጸደ ነፍስም ያሉ) ሰዎች እና በላይ በሰማይ ያሉ ቅዱሳን መላእክት የሚፈጽሙት የድኅነት አገልግሎት ሲኾን ጌታችንን ከዚህ ተራ ማስገባት ካለማወቅ ደጅ የተገኘ ስሕተት ከመኾን አይዘልልም፡፡
ጌታችን በሞት ላይ ያለውን ሥልጣን በተመለከተ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በገዛ ሥልጣኑ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሣ እንላለን፡፡ ወደ መቃብር የወረደው ትስብእት መለኮት የተዋሐደው ነፍስ የተለየው ነው፡፡ ሲነሣም አስነሺ አላስፈለገውም፡፡ እግዚአብሔርነቱ አስነሣው ለማለት በሐዋርያት ቃል እግዚአብሔር አስነሣው ተብሎ ይገለጣል፡፡ "እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና" እንዲል፡፡ ሥራ ፪፥፳፬። እግዚአብሔር ሲል አብን ብቻ ማለቱ አይደለም እግዚአብሔርነት የሦስቱም ነውና፡፡ አብ አስነሣው የሚል ቢገኝ እንኳ በአንድነታቸው ምክንያት እንጂ አንዱን ተነሺ ሌላውን አስነሺ ለማለት አይደለም፡፡ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና ማለቱን ልብ እንበል፡፡ ሞት ሊይዘው ያልቻለ መለኮት የተዋሐደው ስለኾነ ነው፡፡ ሰውየው ግን "ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ሰው ስለኾነ ሰውነትን ስለተዋሐደ በተለይም አብ ያስነሣዋል" በማለት ያልተጻፈ ያነብባሉ፡፡
"በአምላክነቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተማላጅ ነው አብሮ ተማላጅ ነው በሰውነቱ ግን አማላጅ ነው" በማለት የክህደቱን ቃል ያዥጎደጉዱታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ፍናፍንት ሃይማኖት የለም፡፡ አዎ ክርስቶስ የፈጠረውን ሥጋ ተዋሕዶ ቀድሞ ፍጡር የነበረ ትስብእት (ሥጋ) አሁን በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ ይታያል፡፡ ይህንንም ቅዱስ እስጢፋኖስ "እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ ዐያለሁ" ብሎ አረጋግጦልናል፡፡ ሥራ ፯፥፶፮። ከመንበረ ጸባዖት አውርደው አማላጅ ሊሉት አንደበታቸው እንዴት ተከፈተ? የእርሳቸው "ኢየሱስ" መንበረ ጸባዖት ያልደረሰ ሌላ ፍጡር መኾን አለበት፡፡ በአብ ቀኝ ያለው ጌታችን ግን እንዲህ ተብሎ አይነገርበትም፡፡
የፈጠረውን ሥጋ ስለተዋሐደ በሰውነቱ ፍጡር ነው እያሉ ሊቀጥሉ ይመስላል፡፡ "ተዋሕዶ አእተታ ለምንታዌ" ያለውን የሊቁን ቃል አልሰሙትም ወይንም አልገባቸውምና እየነጣጠሉ በአምላክነቱ በሰውነቱ ይላሉ፡፡ ተዋሕዶ ኹለትነት አጠፋ ማለት እንዲህ ነው፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ አይነጣጠልም አይከፋፈልም፡፡ ስለዚህ "በሰውነቱ አማላጅ ነው" ማለት ፍጹም ክሕደት ነው፡፡ በሥጋ ሞተ በመለኮቱ ሕያው ኾነ የሚለው የቅዱስ ጴጥሮስ ቃል ስላልገባቸው ከኾነ ሰው ሥጋው ሲሞት ነፍሱ እንደማትሞተው ማለት እንደኾነ ይወቁ፡፡ ፩ጴጥ ፫፥፲፰። ነፍስ ሞት ስለማይስማማት አትሞትም፡፡ መለኮትም ሞት ስለማይገዛው በመለኮቱ ሕያው ይባላል፡፡ ያንን እየመነዘሩ ለሌላው ለማከፋፈል መሞከር ሐራጥቃነት ነው፡፡
"ዛሬም ኪሩቤል ላይ ኾኖ እየወደቀ እየተነሣ እያለቀሰ ማለት አይደለም፤ በጌቴ ሴማኒ እኔ እና አንተ አንድ እንደኾንን አንድ ይኹኑ ያለው፤ በቀራንዮ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ያለው አንድ ጊዜ የጮኸው ለዘለዓለም ሲጮኽ ይኖራል፡፡ ለሚያምኑ ዛሬም ትኩስ ነው፡፡" በማለት ክህደታቸውን ወደ ፍጹምነት ለማድረስ ይጣጣራሉ፡፡ እርስ በእርሱ የሚጋጭ የደነገጠ ቃል ስለኾነ እርጋታ የለበትም፡፡ በአንድ በኩል "ዛሬም ኪሩቤል ላይ ኾኖ እየወደቀ እየተነሣ እያለቀሰ ማለት አይደለም" ይላሉ አልፈው ደግሞ "ለዘለዓለም ሲጮኽ ይኖራል" በማለት ማጣፊያ ያጥራቸዋል፡፡ "ለዘለዓለም ሲጮኽ ይኖራል" ከተባለ መውደቅ መነሣቱ ዛሬም አለ ማለት ነው፡፡
እኛ የምንለው ቀድሞም መውደቅ መነሣት አልነበረበትም፣ ለአንድ ጊዜም ቢኾን ሲኾን እርሳቸው ግን "አንድ ጊዜ ያደረገው ለዘለዓለም ሲጮኽ ይኖራል" ይላሉ፡፡ ጩኸቱ እስካለ ድረስ አንድ ጊዜም ኾነ ከዚያም በላይ ቢጮህ የሚገኘው ሁሉ የጩኸቱ ውጤት ነው ብሎ ማመን እስካለ ድረስ ኦርቶዶክሳዊ ሙልጭ ያለ የሐራጥቃ ኑፋቄ ስለኾነ አንቀበለውም፡፡ ብቻ እንኳን ለየልዎ፡፡ ፈልገውት ሳይኾን ተገድደው የተናገሩት እንደኾነ አምናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይማርዎ፣ ከጽኑው እሥራት ይፍታዎ!
እንዲያው ለጊዜው እንጂ በአፍም በመጣፍም ገና እንመለስበታለን፡፡ ይቆየን!


1 comment:

  1. ወንድማችን አባይነህ ካሴ ቃለ ህይወት ያሰማልን። መልካም ትምህርት ነው የተማርነው።
    ወልደትንሣኤ አያልነህ ሌላው ይቅርና በእግዚአበሔር እንኳን የሚያምኑ አይመስለኝም። እጅግ በጣም ጮካ፣ ከኪስ አውላቂ የቀለጠፉ ጮሌ፣ ምንም አይነት መንፈሳዊነት የሌላቸው ነጣቂ ናቸው። እሳቸውና ኒወዮርክ ያሉት ሰውየ ኢሕአፓ የነበሩ ኮሚኒስቶች (ተዋሕዶን መጥላት ከኮሚኒስት ርእዮተዓለም ጋር የተጎነጩ) እንደሆኑ ነው የሚገባኝ። በነሱ ቤት ዓለምን ነፃ የሚያወጣው የምእራቡ አስተሳሰብ እንጂ የእግዚአበሔር እምነት አይደለም። ኃይለሚካኤል።

    ReplyDelete